ዜና በዓለ ሢመተ ጵጵስና

የብፁዕ አቡነ ኤልያስ የኖርዲክ እና ግሪክ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ 45ኛ ዓመት በዓለ ሢመት የሀገረ ስብከታቸው መንበረ ጵጵስና በሆነው ስቶክሆልም ከተማ ሐምሌ 12 ቀን 2018 ዓ ም በደማቅ ሁኔታ ተከበረ። ዕለቱ ልክ የዛሬ 45 ዓመት ጵጵስና የተቀበሉበት ቀን በመሆኑ ለበዓሉ የበለጠ ድምቀት እንዲኖረው አድርጎታል።
በበዓሉ ላይ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የኢጣሊያ እና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ መልአከ መዊዕ ልሳነወርቅ ውቤ የጀርመን እና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ፣ መ/ሃይማኖት ቀሲስ ዶ/ር አንዷለም ዳግማዊ የቴክሳስና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ፣ መ/አሚን ለማ በሱፈቃድ የኖርዲክና ግሪክ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ፣ የሀገረ ስብከቱ የክፍል ኃላፊዎች ፣የአድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ፣በመላዋ ኖርዲክ የሚገኙ ዲያቆናት፣ ከተለያዩ አጥቢያዎች የመጡ የየሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባኤ አባላት ተወካዮች እና ምእመናን በበዓሉ ላይ ታድመዋል።

ከበዓሉ ሁለት ቀናት ቀደም ብሎ የሀገረ ስብከቱ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔና የኖርዲክ ዲያቆናት ጉባኤ ብፁዕነታቸው በተገኙበት ተካሂዷል። የብፁዕነታቸው በዓለ ሢመት ሐምሌ 12 ቀን ከሌሊቱ 10 ሰዓት ጀምሮ በመንበረ ጵጵስናቸው ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን በማሕሌት፣ በቅዳሴ እንዲሁም በትምሕርተ ወንጌል የተከበረ ሲሆን ፣ ከምሣ በኋላ ደግሞ ለበዓሉ በተዘጋጀው ልዩ አዳራሽ ለብፁዕነታቸው የክብር አቀባበል ከተደረገ በኋላ በዓሉ በጸሎተ ወንጌል ተጀምሯል።በመቀጠልም በሀገረ ስብከቱ ዲያቆናት፣በስቶክሆልምና አካባቢው ሰንበት ት/ ቤቶች አንድነት ወረብና የተለያዩ ያሬዳዊ ዝማሬዎች ቀርበዋል። የብፁዕነታቸውን ሰፊ አገልግሎት የሚዳስስ የዶክመንቴሪ ፊልም ተዘጋጅቶ የቀረበ ሲሆን ይህ ዝግጅት በተለይ ወጣቱ ትውልድ ብፁዕነታቸውን በደንብ እንዲያውቃቸው አድርጓል።

ብፁዕነታቸውን በቅርብ የሚያውቋቸው፣ በአገልግሎት ለብዙ ዘመናት አብረው የቆዩ አባቶች ብፁዕነታቸው ምን ያህል አዛኝ እና እንደ እናት የሚራራ ልብ እንዳላቸው በእንባ የታጀበ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

በሀገረ ስብከቱ ካሉ ሊቃውንት እና ከኢትዮጵያ ደግሞ በቪዲዮ ለብፁዕ አባታችን መወድስ ቅኔ የቀረበ ሲሆን ይህ ደግሞ በውጪው ዓለም ለሚኖረው ምእመናን እና ለተተኪው ትውልድ እጅግ የሚማርክ ለበዓሉም ከፍተኛ ድምቀት ሆኖ አምሽቷል።

በመጨረሻም ብፁዕነታቸው ምክራቸውን፣ ቃለ ምዕዳን እና ቡራኬ ሰጥተው በዓሉ በሚያምር ድባብ ተፈጽሟል።

የብፁዕ አባታችንን በረከት ለሁላችንም ያድለን።

የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት