ለዓሥር ዓመታት ያህል ተለያይተው የነበሩት አድባራት አንድ ሆኑ!

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በኖርዲክና ግሪክ ሀገረ ስብከት በስዊድን ሉንድ ከተማ ቀደም ሲል ከቅዱስ ሲኖዶስ አንድነት በፊት በተፈጠረ አለመግባት ከዓሥር ዓመታት በላይ ተለያይተው የቆዩት የሉንድ ደብረ ምጥማቅ ቅድስት ማርያምና የሉንድ ደብረ መዊዕ ቅዱስ ሚከኤል አብያተ ክርስቲያናት የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ አረጋዊው ብፁዕ አቡነ ኤልያስ እና የሀገረ ስብከቱ ኃላፊዎች እንዲሁም የሁለቱም አድባራት ካህናትና በርካታ ማኅበረ ምዕመናን በተገኙበት ሚያዝያ 11 ቀን 2018 ዓ.ም. አንድነታቸውን አውጀዋል።
ሀገረ ስብከቱ በ2010 ዓ.ም. በአዲስ መልክ ሲዋቀር ቀደም ሲል በልዩነቱ ወቅት በተወሰኑ አድባራት መካከል ተፈጥረው የነበሩ መንፈሳዊና ማህበራዊ ችግሮችን የሚፈታ የሰላም ኮሚቴ እንዲቋቋም ብፁዕነታቸው በሰጡት መመሪያ መሠረት በሀገረ ስብከቱ ሥር የተቋቋመው የሰላም ኮሚቴ በርካታ ችግሮችን ሲፈታ የቆየ ሲሆን ይህ ሰላም እንዲመጣ ለረጅም ጊዜ በሁለቱ አድባራት መካከል ሰፋ ያለ ምክክርና ውይይቶችን በማድረግ ሁለት የነበሩት አድባራት ተዋሕደው የሉንድ ደብረ ምጥማቅ ቅድስት ማርያም ወቅዱስ ሚካኤል ተብለው እንዲሰየሙ በመስማማት መንፈሳዊ አገልግሎታቸውን በሰላምና በፍቅር ለማከናወን ተስማምተው የአንድነት በዓላቸውን አክበረዋል።
በወቅቱም ሁለቱንም አብያተ ክርስቲያናት የማምለኪያ ቦታ በመፍቀድና ልዩ ልዩ ድጋፍ ሲያደርግ የቆየው በስዊድን ቤተክርስቲያን የሉንድ ካቴድራል ዲን ሬቨረንድ ኒክላስ ብሎደር (L. M. Niclas Blåder) በበዓሉ ላይ ተገኝተው በአብያተ ክርስቲያናቱ አንድነት የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው ወደፊትም ድጋፋቸው እንደሚቀጥል ቃል ገብተዋል።