ልዩ የወላጆች ስልጠና ተጀመረ፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የኖርዲክ እና ግሪክ ሀገረ ስብከት የሰ/ት/ቤቶች አንድነት ለ8 ሳምንታት የሚቆየው “ዘመኑን የዋጀ ተተኪ ኦርቶዶክሳዊ ተዋሕዶ ትውልድ መፍጠር” በሚል መሪ ቃል ለወላጆች የተዘጋጀው ስልጠና ሰኞ የካቲት 17 ቀን 2017 ዓም ተጀምሯል። በመጀመሪያው ቀን ከ325 በላይ ቤተሰቦች የተሳተፉ ሲሆን፣ ከሀገረ ስብከቱ ውጪም በተለያዩ የአውሮፓ አገሮች የሚኖሩ ወላጆች ጭምር የተሳተፉበት ስልጠና እንደነበር ለማወቅ ተችሏል።
ይህ ስልጠና ዘመኑን የዋጀ ተተኪ ኦርቶዶክሳዊ ትውልድን ለመፍጠር ታስቦ የተዘጋጀ ሲሆን፣ በርካታ እውቅ ባለሙያዎችና ሰባኪያነ ወንጌል የሚሳተፉበት ነው። የመጀመርያው ቀን ስልጠና «የምንኖርበት ሀገር ነባራዊ ሁኔታ፣ ተግዳሮቶች እና መልካም አጋጣሚዎች” በሚል ርዕስ በዶክተር ተክሉ አባተ፣ በካይሮ የአሜሪካን ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር አማካኝነት ሰፊ ስልጠና ተስጥቷል። በገለጻቸውም በዚህ በምንኖርበት ክፍለ ዓለም ልጆችን (ከመዋዕለ ሕጻነት እስከ ዩኒቨርሲቲ) ተተኪ ኦርቶዶክሳዊ አድርጎ ማሳደግ ያለበትን ተግዳሮቶች በሰፊው ያስረዱ ሲሆን፣ የመፍትሄ ሀሳቦችንም አስቀምጠዋል። በማስከተል ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች መልስ እና ማብራርያ ሰጥተዋል።
ይህ የስልጠና መርሐግብር በዚህ በአለንበት ክፍለ ዓለም ልጆችን በእውቀት እና በመረጃ በተደገፈ እንዴት ተተኪ ኦርቶዶክሳዊ ትውልድ አድርጎ ማሳደግ እንደሚቻል የሚያሳይ ስለሆነ፣ ወላጆች ጊዜአቸውን አመቻችተው እንዲከታተሉት የሀገረ ስብከቱ የሰ/ት/ቤቶች አንድነት መንፈሳዊ ጥሪ አቅርቧል።