በኖርዌይ ስታቫንገር ከተማ አዲስ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ተገዝቶ ተባረከ።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በኖርዲክና ግሪክ ሀገረ ስብከት በኖርዌይ ስታቫንገር ከተማ የደብረ ገነት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ተገዝቶ የካቲት ፲፭ እና ፲፮/ ፳፻፲፯ ዓ/ም የኖርዲክና ግሪክ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ መልአከ አሚን ቀሲስ ለማ በሱፍቃድ፣ ከተለያዩ ሀገሮች የመጡ ሊቃውንት እና ምእመናን በተገኙበት በብፁዕ አቡነ ኤልያስ የኖርዲክና ግሪክ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ተባርኳል።
በወቅቱ ለግዢው የወጣውን የጨረታ ውድድር አሸንፎ መግዛት እንደተቻለ የደብሩ ሰበካ ጉባኤ ሪፖርት የገለጸ ሲሆን ለዚሁ የተባበሩትን ሁሉ አመስግነዋል።
የስታቨንገር ደብረ ገነት መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን በ1994 እ.ኤ.አ የተመሠረተ ሲሆን በወቅቱ በነበሩት ጥቂት ኢትዮጵያውያን ምእመናን ጥያቄና ተነሳሽነት ነበር።
ለሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ ግዢ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ላበረከቱ ምእመናን የምስክር ወረቀት እና ልዩ ልዩ ስጦታ የተሰጠ ሲሆን በዕለቱ የተገኙት የስታቫንገር ከተማ ከንቲባ እንዲሁም አማርኛ ቋንቋ ሁሉ የሚናገሩ ኖሮጂያን የሀገሪቱ ተወላጆች በበዓሉ በእንግድነት ከመታደማቸውም በተጨማሪ ቤተ ክርስቲያን በመገዛቱ ደስታቸውን ገልጸዋል፣ በቤተ ክርስቲያኑ ምሥረታ ሐሳብ ላይም የዚያን ጊዜው የሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ እና በወቅቱ የሦስተኛው ፓትርያርክ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖት ልዩ ፀሐፊ የነበሩትና የአሁኑ የሀገረ ስብከታችን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኤልያስ መመሪያ ሰጪነት ቤተ ክርስቲያኑ እንደተተከለ ከታሪክ ማኅደር ለማወቅ ተችሏል።
በተያያዘ በደብሩ እስካሁን ሲማሩ የነበሩ ሰባት አዳጊ ልጆች የዲቁና ማዕረግ ከብፁዕ አቡነ ኤልያስ ተቀብለዋል።
በመጨረሻም የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ ቤተ ክርስቲያን በመዛታችሁ ልትመሰገኑ ይገባችኋል፣ በርቱ ልጆቻችሁን በሚገባ ሃይማኖታችንን ልታስተምሩ ይገባል ካሉ በኋላ፣ ነገር ግን አንድነታችሁን፣ ፍቅራችሁን አፅንታችሁ ተገልገሉበት ብለዋል።