የበዓታ ለማርያም ዓመታዊ ክብረ በዓል በኖርዌይ ቴሌማርክ ፖሽግሩን በድምቀት ተከበረ

የበዓታ ለማርያም ዓመታዊ ክብረ በዓል በኖርዌይ ቴሌማርክ ፖሽግሩን በድምቀት ተከበረ።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በቴሌማርክ ኖርዌይ ዓመታዊው የታህሳስ በዓታ ለማርያም ክብረ በዓል ታህሳስ 4 እና 5 ቀን 2017 ዓ.ም በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት በድምቀት ተከበረ።

በቤተ ክርስቲያናችን ከሚከበሩ ደማቅ የእመቤታችን በዓላት መካከል በ3 ዓመት እድሜዋ ታህሳስ 3 ቀን ወደ ቤተ መቅደስ የገባችበት በዓታ ለማርያም (በተለምዶ ታህሳስ በዓታ) ዋነኛው ነው፡፡ ይህ በዓል ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት በትንቢት እንደተናገረው (መዝ. 44፥10)፣ ስምዒ ወለትየ ወርእዪ፣ ወአጽምዒ እዝነኪ፤ ርስዒ ሕዝበኪ ወቤተ አቡኪ፣
እስመ ፈተወ ንጉሥ ሥነኪ፣ እስመ ውእቱ እግዚእኪ –
«ልጄ ሆይ ስሚ፣ ተመልከች ጆሮሽንም አዘንብይ፡፡ ወገንሽን የአባትሽን ቤተ እርሺ፡፡
ንጉሥ ውበትሽን ወዷልና፣ እርሱም ጌታሽ ነው»፡፡

በዚህ የትንቢት ቃል መሠረት አማናዊት ቤተ መቅደስ ድንግል ማርያም ወደ ኦሪት ቤተ መቅደስ የገባችበትን ልዩ ቀን በቤተ ክርስቲያናችን ቅዱስ ትውፊት መሠረት በታህሳስ 3 ቀን በድምቀት ታከብረዋለች፡፡

በኖርዌይ ቴሌማርክ እና ቬስትፎል የበዓታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ይህን የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዓል በድምቀት ለማክበር፣ በአካባቢው ያሉ ምእመናን፣ ከኦስሎ መካነ ቅዱሳን ቅዱስ ገብር ኤል ወአቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን፣ ከክርስቲያንሳንድ ምክሐ ደናግል ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን እና ከሌሎችን አጥቢያዎች የመጡ ምእመናን በተገኙበት በድምቀት ተክብሯል።

በመርሐ ግብሩ ላይ ብጹዕ አቡነ ሕርያቆስ የጣልያን እና አካባቢው ሀገረ ስብከት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ የቅዱስ ሲኖዶስ አባል በተገኙበት፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን መልአከ ሰላም አበበ ገላው (ከደብረ ሰላም መድኃኔ ዓለም፣ ስቶክሆልም)፣ መልአከ ሕይወት ፍስሐ ድንበሩ (ደብረ ምጥማቅ ቅድስት ማርያም፣ ፓሪስ)፣ መምህር አብርሃም (ደብረ ገነት መድኃኔ ዓለም ፣ ስታቫንገር)፣ ቀሲስ ዶ/ር መላኩ (መካነ ቅዱሳን ቅዱስ ገብርኤል እና አቡነ ተክለ ሃይማኖት፣ ኦስሎ)፣ እንዲሁሉም ዲያቆናት በተገኙበት በልዩ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት፣ በዋዜማ፣ በማኀሌት፣ በቅዳሴ፣ በንግሥ ተከብሯል።

በቴሌማርክ ቬስትፎልድ በዓታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ከተመሠረተች ገና 3 ዓመት እንደሆነ ተገልጿል።