የኅዳር ጽዮን ዓመታዊ በዓል በኖርዌይ ክርስቲያንሳንድ በደማቅ ሁኔታ ተከበረ

የኅዳር ጽዮን ዓመታዊ በዓል በኖርዌይ ክርስቲያንሳንድ በደማቅ ሁኔታ ተከበረ።

በኖርዌይ ክርስቲያንሳንድ ምክሐ ደናግል ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የ2017 ዓ.ም የኅዳር ጽዮን ማርያም ከተለያዩ የአውሮፓ አገሮች የመጡ ካህናት፣ ዲያቆናትና ከተለያዩ የኖርዌይ ከተሞች የመጡ ምእመናን በተገኙበት ከዐርብ ኅዳር 20 እስከ እሑድ ኅዳር 22 ቀን 2017 ዓ.ም በደማቅ ሁኔታ ተከበረ። በዓሉ በመላ ኢትዮጵያ በእመቤታችን በተሰየሙ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትና ገዳማት፣ በይበልጥ በአክሱም ጽዮን በየዓመቱ ኅዳር 21 ቀን ይከበራል። በዓሉ የሚከበረው እግዚአብሔር አምላካችን ለሙሴ የሰጠውን የሕዝቡ መመሪያ የተጻፈባትንና የእስራኤል ኃይል የነበረችውን ታቦተ ጽዮን በፍልስጤም ሀገር ጣዖቱን ዳጎንን የሰባበረችበትን ለማሰብ ነው። በዋናነት ደግሞ በንግሥት ሳባ ዘመን በሌዋውያን ካህናትና በንጉሥ ምኒልክ አማካኝነት ታቦተ ጽዮን ወደ ኢትዮጵያ መጥታ በአክሱም ጽዮን የደረሰችበትን ቀን ለመዘከር ነው። በኋላ ዘመን ደግሞ እውነተኛዋ ታቦት እመ አምላክ ወደ ኢትዮጵያ መጥታ በአክሱም ከታቦተ ጽዮን ጋር የተገናኙባትና በወቅቱም በአክሱምና በአካባቢዋ የታየውን አስደማሚ ክስተት የሚታሰብበት ታላቅ በዓል ነው።

በዓሉ የእመቤታችን አጥቢያ ባለበት ሁሉ እንደመከበሩ፣ በውጭው ዓለም በኖርዲክ አና ግሪክ ሀገረ ስብከት በሚገኘው በክርስቲያንሳንድ የምክሐ ደናግል ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ኖርዌይ በሥርዓተ ቅዳሴ፣ በሥርዓተ ማኅሌት፣ በመዝሙር፣ በስብከተ ወንጌል አገልግሎቶች ተከብሯል። የኖርዲክ አና ግሪክ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅና በፊንላንድ የሄልሲንኪ ደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ መልአከ አሚን ቀሲስ ለማ በሱፍቃድ በበዓሉ ተገኝተው የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ሰጥተዋል። በትምህርታቸውም “ ጽዮንን ባሰብናት ጊዜ አለቀስን “ በሚል ርዕስ እሥራኤል ዘሥጋ በስደት በባቢሎ በነበሩ ጊዜ ታቦተ ጽዮንን በማሰብ ያለቀሱትን ለቅሶ በማንሳት እኛም በስደት ስንኖር ሁል ጊዜ ቤተ ክርስቲያንን በማሰብ የሚገባንን ተግባር በመተግበር ልንኖር ይገባል በማለት ሰፋ ያለ ትምህርት አስተምረዋል።

በተያያዘ በበዓሉም ላይ፣ አዚሁ ኖርዌይ ሀገር ተወልዳ ያደገችውና በክርስቲያንሳንድ የምክሐ ደናግል ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ፍሬ የኾነችው የ16 ዓመት አዳጊ ወጣት በዘማሪት መቅደላዊት ኤፍሬም የተዘጋጀው የአማርኛ መዝሙራት ቅጽ በአባቶች ካህናት ተባርኮና ተመርቆ ተለቋል። ዘማሪዋ ይህን መዝሙር አሳትማ ሙሉ ገቢው ባደገችባት ክርስቲያንሳንድ ለምክሃ ደናግል ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያኑ የሕንጻ አሠሪ ኮሚቴ እንዲውል በስጦታ አበርክታለች።

የኅዳር ጽዮን ዓመታዊ በዓል በኖርዌይ ክርስቲያንሳንድ የምክሐ ደናግል ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ሲከበር ይህ ለ15ኛ ጊዜ መሆኑ ታውቋል።

የሀገረ ስብከቱ ሕዝብ ግንኙነት ክፍል