“የመስቀሉ ነገር” (፩ኛ ቆሮ.፩፥፲፰)
በመ/ር ተመስገን ዘገዬ (የገነተ ኢየሱስ ገነተ ማርያም ቤተ ክርስቲያን ሰባኬ ወንጌል)
ነገረ መስቀል ማለት የክርስቶስን መከራ የሚነገርበት፣ የሰው ልጅን ድኀነት የሚገልጽ ትምህርት ነው። ቅዱስ መስቀል በእርሱ ላይ የተሰቀለውን እግዚአ ኃያላን ጌታችን ክርስቶስን ያሳስበናል፡፡ መስቀል የሲኦል መሠረት የተናወጠበት፤ በሰውና እግዚአብሔር መካከል ለዘመናት የነበረው የጠብ ግድግዳ የተናደበት፣ ሞት ድል የሆነበት፣ የትንሣኤውን መንገድ ያየንበት ልዩ መንፈሳዊ ምስጢር ነው፡፡ በየበዓላቱ የመስቀሉ ነገር ሲዘከር በክርስቲያኖች ልብ ውስጥ ልዩ የመንፈስ ደስታ ይፈጥራል፡፡ ይህም አስቀድሞ በነቢያት፣ ከዚያም በሐዋርያት፣ ቀጥሎም በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ዛሬም በመምህራን እየተዘከረ እየተመሰጠረ ይኖራል።
ለአብነት ለመጥቀስ ያህል ከነቢያት ቅዱስ ዳዊት “…ወወሀብኮሙ ትእምርተ ለእለ ይፈርሁከ ከመ ያምሥጡ እምገጸ ቅስት፤ ወይድኀኑ ፍቁራኒከ – ከቀስት ፊት ያመልጡ ዘንድ ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠሃቸው” (መዝ፶፱፡፬ ) እንዳለ መስቀል የድኀነት ምልክታችን ከጠላት ቀስት ማምለጫችንና መሠወሪያችን እንደሆነ ተንብዩዋል፡፡ በሐዲስ ኪዳንም ቅዱስ ጳውሎስ “ እሰመ ነገረ መስቀሉሰ እበድ ውእቱ በኀበ ኀጉላን ወበኀቤነሰ ለእለ ድኀነ ኀይለ እግዚአብሔር ውእቱ፤ የመስቀሉ ነገር ለሚጠፉት ሞኝነት ፤ ለእኛ ለምንድነው ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና” (፩ኛቆሮ.፩፡፲፰) በማለት የመስቀሉ ነገር የእግዚአብሔር ኃይልና ጥበብ እንደሆነ ያስተምረናል፡፡
ከሊቃውንትም ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ስለመስቀል ኃይል ሲናገር “መስቀል የክርስቲያኖች ተስፋ ነው፤ መስቀል የሙታን ትንሣኤ ነው፣ መስቀል የዕውራን መሪ ነው፡ መስቀል ተስፋ ቅቡጻን ነው፣ መስቀል ትንቢተ ነቢያት ነው፣ መስቀል ስብከተ ሐዋርያት ነው፣ መስቀል ክብረ ሰማዕታት ነው፡ መስቀል የጻድቃን ሞገስ ነው፡መስቀል የመነኮሳት ጽሙና ነው፣ መስቀል የድናግል ንጽሕና ነው፣ መስቀል የቤተ ክርስቲያን መሠረት ነው፣ መስቀል የዓለም መረጋጋት ሰላምም ነው፡፡” (ግብረ ዮሐንስ አፈወርቅ.ቅፅ-፪) በማለት በነቢያት የተነገረውን ትንቢት፣ በሐዋርያትም የተነገረውን የመስቀልን ትርጉም ሊቁ ተንትኖ አብራርቶታል።
በተጨማሪም ቅዱስ ዮስጢኖስ ሰማዕትም ስለመስቀል እንዲህ አለ። “አንተ ሰው ለአንድ አፍታ አስብ፤ የዓለሙ ተግባር ሁሉ ያለ መስቀል ይከናውን እንደሆነ ራስህን ጠይቅ። ያለዚህ የድል ምልክት ባሕርን መሻገር አይቻልም። ያለ እርሱ ቈፋሪዎችና ጥበበኞች ቅርፅ ሥራዎችም አይሰሩም። የሰው ቅርፅ ራሱ መስቀል ነውና፤ አዕዋፍም እንደመስቀል ሁነው በአየር ይበራሉ” (st.Justin martyr the first Apology chapter-፶፭)
እንዲሁም ቅዱስ ቄርሎስ ዘኢየሩሳሌም “ስለተሰቀለው ክርስቶስ ለመመስክር ማፈር የለብንም። መስቀሉን ማኀተማችን በማድረግ፣ በግንባራችን በእጃችንና በማንኛውም ነገራችን ላይ በማድረግ፣ እንዲሁም በምንበላው ዳቦ ላይ በምንጠጣው መጠጫችን በማማተብ፣ ስንወጣና ስንገባ፣ ከመተኛታችን በፊትና ነቅተን ስንነሣ፣ በምንጓዝበትና በምናርፍበት ጊዜ ሁሉ የክርስቶስን መስቀል በግልጽ ማማተብ አለብን።”ይላል (st.cyril of Jerusalem catecheses xiii;36)
ከላይ እንዳየነው መስቀል በብሉይ፣ በሐዲስ እንዲሁም በሊቃውንት ሲነገር ቢቆይም፣ በዘመናችን የሚነሱ የሚገቡ ፍሬ ሀሳቦችን አንስቶ እንደሚከተለው ማብራሪያ መስጠት ያስፈልጋል።
1. የመስቀል ምንነት
መስቀል ብዙ በሽተኞች የተፈወሱበት፣ ብዙ ሙታንን የተነሱበት፣ ታላላቅ ተአምራት የተከናወኑበት ነው። ለዚህም ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚከተለው ይገልጹታል።
- መስቀል ልዑል እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያለውን ፍቅር የገለጠበት (ፊል. ፪፡፰፣ ፩ኛ ዮሐ.፬÷፱፣ ዮሐ.፫÷፲፮)
- መስቀል የክርስቶስ ሥጋና ደም የተፈተተበት(መጽሐፈ ምሥጢር ዘአባ ጊዮርጊስ ፭ ቁ፳፰)
- መስቀል ሰውና ልዑል እግዚአብሔር የታረቁበት(፪ኛ ቆሮ. ፭፡፲፱ ኤፌ. ፪፡፲፬)
- መስቀል የሰው ልጅ ከኃጢአት ነጻ የወጣበት(ሮሜ ፮፡፳፪ )
- መስቀል የሞት ኃይል የተሻረበት(ዕብ. ፪፡፲፬-፲፭፣ ፪ኛ ጢሞ.፩፡፲)
- መስቀል የሰው ልጅ ድኀነት የተፈጸመበት(፩ኛጴጥ ፪፡፳፬)
- መስቀል ሰይጣን ድል የተደረገበት (ቆላ. ፩፡፳)
- መስቀል ሰላም ያገኘንበት (ቆላ. ፩፡፳)
- መስቀል ለምናምን ኃይላችን ነው፡፡(፩ኛ ቆሮ.፩፡፲፰)
በመሆኑም መስቀል የአጋንንት ድል መንሻ ወይም የርኩሳን መናፍስት መቅጫ ንዋየ ቅዱስ ነው፡፡ ድውያነ ሥጋም ሆነ ድውያነ ነፍስ የሚፈወሱበት ፍቱን መድኃኒት ነው፡፡ ሰማያዊያን መላእከት ምድራዊያን ካህናት አገልግሎት የሚፈጽሙበት ኃይል ነው፡፡ የቅድሰት ቤተ ክርስቲያን አክሊል፣ የገዳማት ዘውዳቸው የክርስቲያኖች ሁሉ የክብር ጌጥ ነው፡፡
2. ለቅዱስ መስቀሉ ስግደት እና ክብር እንዲገባ
ለቅዱስ መስቀሉ የጸጋና የአክብሮት ስግደት፤ አስተብርኮና አድንኖ ማቅረብ እንደሚገባ ቅዱስ ዳዊት እንዲህ በማለት ይናገራል “ወንሰግድ ውስተ መካን ኀበ ቆመ እግረ እግዚእነ፤ እግሮቹ በቆሙበት ሥፍራ እንሰግዳለን” (መዝ.፻፴፩፥፯)። ይህንንም ሊቁ ቅዱስ ያሬድ “ለመስቀልከ ንሰግድ ኦ ሊቅነ ወለትንሣኤከ ቅድስት ንሴብሕ ኵልነ” (ጾመ ድጓ) ብሎ ገልጾታል። ይህንንም ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ተግባራዊ በማድረግ ለመስቀል ከዜማ ጋር የአክብሮት ስግደት ሥርዐት ሰርታ ስታከናውን ኖራለች፣ እየፈጸመችም ትገኛለች። የዚህም ምክንያት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ቅዱስ መስቀሉን አካሏ የሆነ ክርስቶስ በቀኖት የተቸነከረበት፣ ደሙ የፈሰሰ፤ ታላላቅ ኃይል የተፈጸመበት በመሆኑ ነው፡፡ በተጨማሪም ቅዱስ ያሬድ በድጓው “…ዮም በዓለ መስቀሉ በሰማያት ወዘነግሠ በምድር ከመ ያብርህ ለአሕዛብ ወለኵሉ ዓለም በፍሥሐ ወበሰላም ወትረ ይሴባሕ በቅዱሳን – ዛሬ የመስቀሉ በዓል በሰማያትም ሆነ በምድርም ከበረ ለአሕዛብና ለዓለም ሁሉ ያበራ ዘንድ ዘወትር ይመሰገናል”ይላል፡፡(መጽሐፈ ድጓ ዘመስቀል ገጽ-24)
በአጠቃላይም ከላይ ቅዱስ ያሬድ እንደገለጸው ሁሉ ነገረ መስቀሉ የማይዘከርበት፣ የመስቀል ክብሩ የማይገለጥበት ሥርዓተ አምልኮት፤ ሥርዓተ ማኀሌትና ሥርዓተ ጸሎት ቤተ ክርስቲያናችን የላትም፡፡ በተለይም ለቅዱስ መስቀሉ በዓመት ሁለት ጊዜ (መጋቢት ፲ እና መስከረም ፲፯) ልዩ ሥነ-በዓል አድርጋ ስታከብረው፣ በየዕለቱም በየሰዓቱ ነገረ መስቀሉን ታስባለች፡፡
3. መስቀል እና የደመራ ትውፊት
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል ዕውር ሲያበራ፣ ሙት ሲያስነሣ ቀናተኞች አይሁድ አይተው እንዲቀበርና ደብዛው እንዲጠፋ ስለወሰኑ፤ የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ጉድፍ (የቤታቸውን ቆሻሻ) እንዲጥሉበት አደረጉ፡፡ ከረጅም ጊዜም በኋላ ቦታው ኮረበታማ ሆነ፡፡ ትውልድ እያለፈ ትውልድ ሲተካ ከጊዜ ብዛት የተነሣ መስቀሉ የተቀበረበት ቦታ ተረሳ።
ነገር ግን የቆስጠንጢኖስ እናት ንግሥት ዕሌኒ የጌታችን መስቀል በኢየሩሳሌም ተቀብሮ ለብዙ ዘመናት መኖሩን ትሰማ ነበር። ንግሥት ዕሌኒም ልጄ ክርስቲያን ቢሆን ከቁስጥንጥንያ ወደ ኢየሩሳሌም ሂጄ የክርስቶስን ቅዱስ መስቀል ከተቀበረበት አስቆፍሬ አስወጣለሁ ብላ ስእለት ተስላ ነበር፡፡ ልጇዋ ቆስጠንጢኖስንም በጥንቃቄ ክርስትናን እያስተማረች አሳደገችው። በተሳለችውም መሠረት ልጇዋ ክርስትናን ተቀበለ፤ ጠላቶቹንም በእግዚአብሔር ኃይል አጥፍቶ በአባቱ ግዛት ላይ ነገሠ። እርሷም የጠፋውን መስቀል እተፈለገች ሳለ ኪራኮስ የሚባል አረጋዊ እንደነገራት እንጨት አስቆርጣ፣ በመስከረም 16 ቀን ደመራ አስደምራ፣ ካህናቱን ካጸለየች በኋላ በእሳት እንዲያያዝ አደረገች። የደመራው (የዕጣኑ) ጢስም መስቀሉ ወደ ተቀበረበት ቦታ አመለከተ፡፡ ይህንንም ሊቁ ቅዱስ ያሬድ “..ዘዕጣን አንፀረ ሰገደ ጢስ በጎልጎታ፤ ዘደፈኑ አይሁድ ዮም ተረክበ ዕፀ መስቀል” (ድጓ) በማለት ዘምሯል ። በዚህ መሠረት ዕሌኒ መስቀሉ የተሰቀበረበትን ተራራ መስከረም ፲፯ ቀን ቁፋሮው አስጀምራ፣ በመጋቢት ፲ ቀን የጠፋው የክርስቶስ መስቀልን አገኘች፡፡ ይህንንም ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ሲያደንቅ “ኮነ ተአምር ወመንክር እስመ ተረክበ ዕፀ መስቀል ክቡር ዘኃሠሠት ዕሌኒ ንግሥት፤ ንግሥት ዕሌኒ የፈለገቸው ክቡር የሆነው ዕፀ መስቀል በተገኘ ጊዜ ተአምርና ድንቅ ነገር ሆነ” (መጽሐፈ ድጓ ዘመስቀል ገጽ-፳፮) ብሏል፡፡
መስከረም 16 ደመራ የተደመረበት እና ቅዱስ መስቀሉ ያለበት ቦታ የታወቀበት፣ ብዙ ርጥብና ደረቅ እንጨት ተሰብስቦ የሚቆምበት የመስቀል ዋዜማ ዕለት ነው፡፡ በዚህ ቀንም ሕዝቡ በየደጃፉ፣ ደመራ ደምሮ በእሳት በመለኮስ በእጁ የችቦ ብርሃን ይዞ ”ኢዮሃ አበባዬ መስከረምዬ ጠባዬ” እያለ በደስታ ይዘክራል፣ ያበስራል፡፡ መስከረም ፲፯ ቅዳሴ ቤቱ የተከበረበት እና ቁፋሮ የተጀመረበት እለት ነው፡፡ ለዚህም በመጽሐፈ ስንክሳር “ይህንንም የከበረ መስቀልንም ዳግመኛ የተገለጠበት መጋቢት ፲ ቀን ነው፡፡ ዜናውንም በዚህ ቀን ጽፈናል ምእመናንም፤ በታላቁ ዐቢይ ጾም መካከል በዓሉን ማክበር ስላልታቻለቸው በዓሉን ቤተ ክርስተያን በከበረችበት ቀን አደረጉ፡፡ ይህም መስከረም ፲፯ ቀን ነው፡፡”ይላል፡፡
4. የደመራ እና ችቦ ምሳሌነት
ሊቁ ቅዱስ ያሬድ “ ዮም መስቀል ተሰብሐ፤ ዮም መስቀል ለአኃው አብርሃ በፍሥሐ ወበሰላም ቅድመ እግዚአብሔር አብጽሐ፤ ዛሬ መስቀል ተመሰገነ፤ ዛሬ መስቀል ለወንድሞቻችን አበራ በሰላምና በደስታ በእግዚአብሔር ፊት አደረሰን” (መጽሐፈ ድጓ ዘመስቀል ገጽ-፬) ይላል፡፡ በመሆኑም የደመራ እና የችቦ የደስታ፣ ብርሃን እና ሰላም ምሳሌነቱ የሚከተለው ነው።
- ደመራው ተደምሮ ጸሎት መደረሱ ንግሥት ዕሌኒ የጌታችን መስቀል ለመፈለግና ምልክት ለማግኘት ሰትነሣ ያደረገችውን ሥነ-ሥርዓት ይወክላል፡፡
- የክርስቶስ መስቀል ለዓለሙ ሁሉ እውነተኛ የነጻነት ብርሃን ሆነ፡፡ እኛም ለእውነተኛ የድኀነት ቀን እንኳን አደረስን ስንል ችቦ እንለኩሳለን፡፡
በአጠቃላይ መስቀል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ከፍተኛ ክብር አለው፡፡ መሠረቱም ከላይ እንደተገለጸው መስቀል በነቢያትም ትንቢትና ምሳሌ፣ በሐዋርያትም አስተምሮ መነሻነት ነው፡፡ በተለይ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “..ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተሰቀለሁበት ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ” (ገላ.፮÷፲፬) እንዲል፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም መስቀል ትምክህቷ መሆኑን ከላይ ጉልላቷ፣ ዙሪያዋን ቅጽሯ፣ ማእከሏን መቅደስ ቀራንዮ በማደረግ የክርስቶስ መከራውን እየተካፈለች እየኖረች ነው። በተጨማሪም በየእለቱ በየዓመቱ የመስቀልን በዓል እየዘከረች ትገኛለች።