በኖርዲክ እና ግሪክ ሀገረ ስብከት የካህናት ጉባኤ ተካሄደ፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በኖርዲክ እና ግሪክ ሀገረ ስብከት የካህናት አገልግሎት ክፍል በሀገረ ስብከቱ የሚያገለግሉ ካህናት እና ዲያቆናት የተሳተፉበት የአንድነት የምክክር ጉባኤ ተካሄደ፡፡
ታኅሣሥ 11 ቀን 2017 ዓ.ም በበይነ መረብ በተካሄደው በዚህ ጉባኤ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የጣልያን እና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የሀገረ ስብከቱ ሥር አስኪያጅ መልአከ አሚን ለማ በሱፈቃድ፣ የሀገረ ስብከቱ አገልግሎት ክፍሎች ኃላፊዎች፣ ሊቃውንት፣ ዲያቆናት ተገኝተዋል፡፡
የካህናት አገልግሎት ክፍል በሀገረ ስብከቱ ያሉ ካህናት የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን መንፈሳዊ አገልግሎት እንዲጠናከር፣ ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን እና ሥርዓት እንዲጠበቅ ለማድረግ በእቅድ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡
በዚህ ጉባኤ የካህናት አንድነት ማኅበር (ጉባኤ) ለማቋቋም መነሻ ሀሳብ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡  የቀረበው ሀሳብ አስፈላጊ መሆኑን በማጽናት ወደተግባር እንዲገባ እና ካህናት ተቀራርበው እንዲያገለግሉ፣ እንዲሁም የቤተ ክርስቲያንን ሕልውና ለማስቀጠል የማይተካ ሚና ስላላቸው አንድነቱ በአጠረ ጊዜ መመሥረት እንዳለበት በጉባኤው ውይይት ተደርጎበታል፡፡
በተያዘ እቅድ መሠረት የኖርዲክ ሀገረ ስብከት የካህናት አንድነት ጉባኤ መመሥረቻ የፊታችን መጋቢት በሚካሄደው 2ኛ ጉባኤ እንደሚካሄድ በካህናት አገልግሎት ክፍል ሓላፊው በቀሲስ ዶ/ር መንግሥቱ ጎበዜ ተገልጧል፡፡
በተጨማሪ የካህናት ሚና በዝርወት ላለችው ቤተ ክርስቲያን በሚል በቅዱስ አግናጥዮስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የሶርያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሴሚናር ዳይሬክተር በቀሲስ ዶ/ር ዮሃነን ሀቢል ልምድ እና ገለጻ ቀርቧል፡፡
ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ቃለ ምዕዳን እና ቡራኬ ሰጥተው ጉባኤው በጸሎት ተፈጽሟል፡፡