በኖርዌይ በርገን ከተማ አዲስ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ተገዝቶ ተባረከ።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በኖርዲክና ግሪክ ሀገረ ስብከት በኖርዌይ በርገን ከተማ የመንበረ ልዑል ቅዱስ ሚካኤል ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ተገዝቶ የካቲት ፰ እና ፱ / ፳፻፲፯ ዓ/ም የኖርዲክና ግሪክ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ መልአከ አሚን ቀሲስ ለማ በሱፍቃድ፣ ከተለያዩ ሀገሮች የመጡ ሊቃውንት እና ምእመናን በተገኙበት፣ በብፁዕ አቡነ ኤልያስ የኖርዲክና ግሪክ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ተባርኳል።
የተገዛው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ምንም ዕዳ የሌለው መሆኑን የገለፁት የደብሩ አስተዳዳሪ መልአክ ጽዮን አባ ሙሴ ለዚሁ የተባበሩትን ሁሉ አመስግነዋል።
የበርገን መንበረ ልዑል ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተው በ2004 እ.ኤ.አ ሲሆን በወቅቱ ከወገኖቻችን ኤርትራውያን ኦርቶዶክሳውያን ጋር በጋራ አገልግሎት ይሰጥ እንደነበር በቀረበው ሪፖርት ተገልጿል። በኋላም ከ 2014 እ.ኤ.አ .ጀምሮ ግን በተጠናከረ መልኩ የቀጠለ ሲሆን በደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ጽዮን አባ ሙሴ ጠንካራ አስተባባሪነት ከብዙ ድካም በኋላ ይህ ዛሬ የተባረከው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያንን ለመግዛት ተችሏል። በተለይ ከኢትዮጵያ ተሠርቶ የመጣው መንበር በሊቃውንቱና በሕዝቡም ዘንድ ከፍተኛ ትኩረት የሳበ ነበር። እንዲሁም አንድ የሊቀ ጳጳሱና ሁለት የአስተዳዳሪዎች የክብር ወንበር ከኢትዮጵያ ተገዝተው መምጣታቸውን ለማውቅ ተችሏል። ለሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ ግዢ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ላበረከቱ ምእመናን የምስክር ወረቀት እና ልዩ ልዩ ስጦታ የተሰጠ ሲሆን በከፍተኛ ክትትል ለዚህ ውጤት ላበቁት ለደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ጽዮን አባ ሙሴም ከአጥቢያው ምእመናን ስጦታ ተበርክቶላቸዋል።
በመጨረሻም የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ ቤተ ክርስቲያን በመዛታችሁ የራሳችሁን አድራሻ አግኝታችኋል፣ በዚህም ልትመሰገኑ ይገባችኋል፣ በርቱ ልጆቻችሁን በሚገባ ሃይማኖታችንን ልታስተምሩ ይገባል ብለዋል።