ማኅሌተ ጽጌ ወደ ፊንላንድኛ ቋንቋ ተተርጉሞ ተመረቀ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለማኅሌት አገልግሎት ከምትጠቀምባቸው መጻሕፍት መካከል አንዱ የሆነው የማኅሌተ ጽጌ መጽሐፍ ወደ ፊንላንድኛ ቋንቋ ተተርጎመ። ይህንን የአባ ጽጌ ድንግል ድርሰት የሆነው መጽሐፍ የተረጎሙት የፊንላንድ ሀገር ዜጋ የሆኑት እና ከሃምሳ ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ለአምስት ዓመታት ቆይታ ያደረጉት አቶ ኒሎ ሆንካነን ናቸው። ተርጓሚው መጽሐፉ ወደ ፊንላንድኛ ለመተርጎም ከ10 ዓመት በላይ ሲያጠኑ እንደቆዩና ዋና ምንጭ አድርገው የተጠቀሙት ደግሞ በ1919 ዓ.ም. በዶ/ር አዶልፍ ግሮህማን የተተረጎመውን የጀርመንኛ ቅጅ እንደሆነ ገልጸዋል።
አቶ ኒሎ ማኅሌተ ጽጌን ለምን ለመተርጎም እንዳነሳሳቸው ሲጠየቁ፤ «ማኅሌተ ጽጌ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካሏት የመዝሙር መጻሕፍት ውስጥ በትንሽ ጥራዝ መጽሐፍ ሆኖ መታተም የሚችል እና መንፈስን የሚያረካ ይዘት ያለው ስለሆነ ነው» ይላሉ። መጽሐፉ በያዝነው መስከረም ወር ውስጥ በፊንላንድ ርዕሰ ከተማ ሄልሲንኪ ከተማ የሄልሲንኪ ደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ካህናት እና ምእመናን፣ የደብሩ ጽጌ ሃይማኖት ሰንበት ት/ቤት መዘምራን የፊንላንድ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ተወካይ እና የተርጓሚው ቤተሰቦችና ወዳጆች በተገኙበት ተመርቋል።