የአህጉረ ስብከቱ መዋቅር
ቃለ አዋዲ
ቃለ አዋዲ የኢትዮጵያ ኦርቶዶስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን አንድነትና አስተዳደር ለማጠናከር የወጣ መንፈሳዊ የአስተዳደር ሕግ እና መመሪያ ነው። ቃለ አዋዲውን በዚህ ማስፈንጠሪያ ያገኙታል
ቅዱስ ሲኖዶስ
በቅዱስ ፓትርያርኩና በብጹአን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቤተ ክርስቲያኑን ዶግማና ቀኖና እንዲሁም ወሳኝ አስተዳደራዊ ውሳኔዎችን የሚሰጥ የበላይ ወሳኝ ጉባኤ ቅዱስ ሲኖዶስ ይባላል። ቃሉ የግሪክ ሲሆን፣ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ስብሰባን ያመለክታል።
የመጀመሪዋ ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ለመጀመሪያ ጊዜ በኢየሩሳሌም የተሰበሰበው የቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ በዘመኑ የነበረችው ቤተ ክርስቲያን የምትመራበትን ደንብ ካወጣ በኋላ “እኛና መንፈስ ቅዱስ ፈቅደናል” (የሐዋ ሥ 15፡- 29) ይላል ። አዎ ጥንታዊ ቤተ ክርስቲያን ሥራዋን ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ትሠራ ነበር። መመሪያ ደንብም በምታወጣበት ጊዜ የመንፈስ ቅዱስ ኃይልና ፈቃድ ከመሪዎችዋ ጋር እንደ ነበረ ከላይ የጠቀስነው ጥቅስ ያረጋግጣል። ከዚህም የተነሳ በየጊዜው ያወጣቻቸው ሕጎች ለጊዜው ብቻ ሳይሆን ለዛሬዋ ቤተ ክርስቲያን ሕግ መመሪያ ሆነዋል። ለምሳሌ፡- ቀሌምንጦስ፣ ዲድስቅልያ፣ አብጥሊስ፣ ግጽውና ሥርዓት ልሎችም የታወቁት መጻሕፍት፣ የመጀመሪያዋ ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን መመርያ ደንቦች እንደ ነበሩ፣ የሥነ ጽሁፋቸው ይዘት ያስረዳል። እነዚህም ሕጎች በስኖዶስ በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ የተሰሩ ስለነበሩ፣ ከተሰራባቸው በኋላ እንዲናቁና እንዲወድቁ አልተደረጉም። እንዲያውም ከቅድሳት መጻሕፍት ገብተው እንዲቆጠሩ ተደርገዋል።
በዚህም አንጻር የዛሬዋ ቤተ ክርስቲያን አባቶች ሊቃነ ጳጳሳት የሚያደርጉት መንፈሳዊ ጉባኤ ሲኖዶስ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር እንጂ በራሳቸው ፈቃድ ብቻ አይደለም። ምክንያቱም በቀድሞዋ ቤተ ክርስቲያን መሪ አበው ላይ ይሠራ የነበረው መንፈስ ቅዱስ ዛሬም በቤተ ክርስቲያን ባሉ መሪ አበው ላይ አድሮ እንደሚሠራ የማይታበል ተስፋ በክርስቶስ ለቤተ ክርስቲያን ተሰጥቷልና።
በመሆኑም የቅዱስ ሲኖዶስ ጉበኤ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የቤተ ክርስቲያንዋ የበላይ መሪና ሕግና ድንብ የሚያወጣ የቅዱስ ፓትርያርኩና የብጹአን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ጉበኤ ነው። ስለዚህ ቅዱስ ሲኖዶስን መከተል ስለ ሰዎች ክብር ሳይሆን ስለመንፈስ ቅዱስ ክብር ይቀበሉታል። በአፈጻጸሙም ሥርዓት ጊዜ የመንፈስ ቅዱስን ፈቃድ እንደመፈጸም አድርገው በሥራ ያውሉት ዘንድ ይገባል።
የኢትዮጳያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በሲኖዶስ የወጣውን መመሪያና ደንብ ለእምነትዋ ወሳኝ ለአስተዳደርዋ መሠረት፣ መጽሐፍ ቅዱስንም ለትምህርትዋ ምንጭ አድርጋ ትሠራለች። ታሠራለች። የሥራ አፈጻጸምዋም በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድና መሪነት እንደሆነ ታምናለች። የቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ የመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ነውና። (ሕገ ቤተ ክርስቲያን ርእስ አንቀጽ የተወሰደ)
ስዊድንና አካባቢ ሀገሮች መንበረ ጳጳስና ሀገረ ስብከት መንፈዊ ጉባኤ አመሠራረት
የመንበረ ጳጳስና ሀገረ ስብከት መንፈሳዊ ጉበኤ አመሠራረት አቁዋም በተመለከተ
- የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኤልያስ የጉባኤው ርእሰ መንበር ሆነው የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅና ዋና ጸሐፊው፣ የየክፍል ኃላፊዎች ጨምሮ፣ በተጨማሪም በሀገረ ስብከቱ ሥር ካሉ ወረዳዎች የወረዳ ሥራ አስኪየጅ እና ከየንኡስ ክፍሉ ኃላፊዎች አንድ አንድ አባላት በአንድነት ተሰብስበው የመንበረ ጳጳስና ሀገረ ስብከት ጠቅላላ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤን ይመሠርታል።
- ጠቅላላ መንፈሳዊ ጉባኤውም በዓመት አንድ ጊዜ ይሰባሰባል።
- ይህ ጠቅላላ ጉባኤም ከመካከሉ በየ 3 ወር 1 ጊዜ የሚሰበሰብ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ይመርጣል። (ቃለ አዋዲ ገጽ43)
ወረዳ ቤተ ክህነት
በሀገረ ስብከቱ ሶስት ወረዳ ቤተ ክህነት አሉ እነሱም፡-
- ስቶኮልም እና ፊላንድ ወረዳ ቤተ ክህነት
- ኖርዌይ ወረዳ ቤተ ክህነት
- ሉንድ ጉተንበርግ እና ዴንማርክ ወረዳ ቤተ ክህነት ይገኙበታል።